120 የታካሚ አልጋዎች የሚኖሩት የዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል G+4 የአይን ህክምና ማዕከል ግንባታ ማጠናቀቂያ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

 

በጤናው ዘርፍ በርካታ ችግር ፈቺ ስራዎችን በመስራት መዲናችንን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ የተያዘውን ሰፊ ውጥን እውን ለማድረግ በአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ባለቤትነትና ክትትል እየተገነባ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል G+4 የአይን ህክምና ማዕከልን ለአገልግሎት ለማብቃት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

በ2,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና 239,573,327.00 ብር የውለታ መጠን የተያዘለት ፕሮጀክቱ 98 በመቶ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን አሁን ላይ የአሳንሰር ገጠማ እየተከናወነለት ይገኛል፡፡

ህንፃው 120 የታካሚ አልጋዎችን ጨምሮ 45 የምርመራ ክፍሎች፣30 የታካሚዎች መከታተያ ክፍሎች፣8 የቀዶጥገና ክፍሎች፣2 የአንስቴዢያ ክፍሎች፣2 የመማሪያ ክፍሎች፣መድሀኒት ቤት፣መሰብሰቢያ አዳራሽ፣የማገገሚያ ክፍል እና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ-ልማቶች ተሟልተውለታል፡፡

የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና በአንድ ጊዜ ለ30 ታካሚዎች ህክምና መስጠት የሚያስችለው የዳያሊሲስ ህክምና ማዕከል በቅርቡ ተጠናቆ በክቡር ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በይፋ መመረቁ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡: የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

Share this Post