8ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር " በአካልና በአእምሮ የዳበረ ትውልድ ለአገር ግንባታ " በሚል መሪ ሀሳብ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ 07 ሮም ሜዳ በድምቀት ተጀመረ ።

 

ዘንድሮ በአዲስ አበበ ከተማ ለ8ኛ ጊዜ የሚካሄደዉ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ዉድድር " በአካልና በአእምሮ የዳበረ ትዉልድ ለአገር ግንባታ " በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 14/2014ዓ.ም ከ 2ሺህ በላይ ተማሪዎች በ7 የስፖርት ዐይነቶች ይወዳደራሉ ።

የአደስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ የሚያዘጋጁት ይህ 8ኛዉ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ዉድድር ዛሬ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በሚገኘዉ #ሮም_ሜዳ /ሁለገብ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራ/ ተጀምሯል ።

በፕሮግራሙ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ባደረጉት ንግግር " ትምህርት ለአንድ ሀገር ቁልፍ የልማትና የዕድገት መሠረት በመሆኑ ፣ ስፖርትም በአካል ፣ በአእምሮና በስነልቦና የታነፀ ትውልድ መፍጠሪያ በመሆኑ እንደ ዋና ግቦችን ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል ።

የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር የነገ የሀገር ተተኪና ታዳጊ ወጣቶችን ማፍለቂያ በመሆኑ ተማሪዎች በቆይታቸው በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነትና ስነምግባር እንዲወዳደሩ በአዳራ ጭምር ያሳሰቡት አቶ ዘላለም ለፕሮግራሙ መሳካት ከትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ፣ ለአስተናጋጁ ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል ረዲ በበኩላቸው የ8ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ክፍለ ከተማችን በአስተናጋጅነት እንዲመረጥ ዕድሉን ለሰጡ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እና ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በነዋሪውና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል ።

የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ውጤታማ ስፖርተኞች ከትምህርት ቤት እንዲፈሩ ከከተማ በወረደው አቅጣጫ መሰረት በክፍል ከተማው ስር ባሉ ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ እንደሚሰራ አቶ ጀማል ረዲ ተናግረዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ በበኩላቸው በ8ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ላይ ከ11ዱ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ተማሪዎች በ7 የስፖርት ዐይነቶች ውድድራቸውን እንደሚያካሂዱ ገልፀዋል ።

አቶ ዳዊት ትርፉ አያይዘውም የውድድሩ ዐላማ የተቀዛቀዘውን የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ማነቃቃት ፣ ተተኪና ታዳጊስፖርተኞችን በየፍላጎታቸውና ችሎታቸው ለማፍራት ከዚህም ባሻገር ከተማ አስተዳደሩና ነዋሪውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለመምረጥ የሚያስችል መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን አብራርተዋል ።

በመክፈቻ ላይ በተለያዩ የኪሎ ካታጎሪ የቦክስ ውድድር የተጀመረ ሲሆን የዕለቱ የክብር እንግዶች አስጀምረዋል

በፕሮግራሙ ላይ በዉድድሩ የሚሳተፉት የ11ዱም ክፍለ ከተማ ስፖርተኞች፣ የከተማዉናየክፍለ ከተማ ከፍተኛ የስራ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸዉ ስፖርተኞችና የስፖርት ቤተሰቦች ታድመዋል ።

Share this Post